Wednesday, April 10, 2013

የተሻለ ምርጫ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
         በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!
እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ መዝ 26፥4
           እስትንፋሰ እግዚአብሔር የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ "የተሻለ ምርጫ" ብሎ ከሚያስቀምጣቸው አንዱ ከላይ የተመለከትነው እፁብ ድንቅ ምርጫ ነው፡፡ ንጉስ ዳዊት በቤተ እግዚአብሔር መኖር በቤተመንግስት ከመኖር ወይም ሌላ ሥፍራ ከመገኘት የተለየ ነገር እንዳለው ተሰምቶታል አውቋልም፡፡
          ብዙ ጊዜ እንስሳዊ የሆነ ባህርያችን ተድላ ሥጋ የሚደረግባቸውን ቦታዎች ይመርጣል፡፡ ብዙ መብልና መጠጥ ያለበት፣ ጨዋታና ሣቅ የነገሠበት ወይም ዕረፍተ ሥጋ(የሥጋ ምቾት) የተሟላበትን ቦታ ይመኛል ይስማማዋልም፡፡ከዚያ የከፋው ደግሞ በጤናማ አእምሮ የማይደረጉና ጊዜያዊ ለፍትወተ ሥጋ እርካታን የሚሠጡ ዲያቢሎስ በቅዱስ እግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን የልጅነት የክብር አክሊል የተደፋለትን የእግዚአብሔር መንፈስ መቅደስ የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ አካል የተባለን የሰው ልጅ የመጨረሻውን ውርደት ለማዋረድ ያዘጋጃቸውን በመዝናኛና ከጭንቀት መገላገያ በሚል ስም የተፈጠሩ ወጥመዶች፡- መጠጥ፣ አደንዛዥ ዕፆች፣ የተፈጥሮን ክብርና ውበት የሚያጎድፍ ድርጊቶች ወዘተ… የሚዘወተሩባቸው ሥፍራዎች መገኘት የሚወዱ በርካታቶች አሉ፡፡ ይህም ውጤቱ ለሥጋ ውድቀት ለነፍስም ውርደት ነው፡፡
         ሥፍራዎቹም ሆኑ የሚፈፀምባቸው ነውር የምንፈልገውን ደስታ አይሠጡንም ይልቁንም ይበልጥ የልማዳችን ባርያ እየሆንን ባዶነታችን እየሰፋ ተስፋ መቁረጣችን እየበረታ ይሔድና ለደስታ ብለን የጀመርነው ህይወት ለመከራ ይዳርገናል፡፡ የተሻለ ምርጫ አለመሆኑን የምንረዳው ምርጫችንን ለማስተካከል አቅማችንም ዕድላችንም ከተሟጠጠ በኋላ ነው፡፡
        በጥንቃቄ ያልተያዘ ምግብ እንደሚበላሽ ጣዕምና መዓዛው እንደሚቀይር ሁሉ በተፈጥሮ የተሠጡንን ስሜቶቻችንን በጥንቃቄ ካላስተናገድናቸው ይበላሻሉ፡፡በትክክል ሊሠጡን የሚገባቸውን እርካታ መስጠት ይሳናቸዋል፡፡ለህይወታችን ቅመም የሆኑት ስሜቶቻችንም ይሞታሉ፡፡ለዚህ ምክኒያቱም "ሁሉ በሥርዓትና በአግባብ ይሁን!" ተብለን የተመከርነውን አለመፈፀማችን ነው፡፡
        በዚህ ዓለም ደስታን ሊሠጡ ይችላሉ ተብሎ የሚታሰቡ ነገሮች በቀላሉ ማግኘት የሚችሉ ሰዎች ተስፋ ቢስ ህይወት ሲመሩ ብሎም ራሳቸውን ሲያጠፉ ሊደንቀን ይችላል፡፡ ምን ነካው? ምን ጎደለበት? ብለን እናስባለን ምክንያቱ ከሥጋው በፊት ስሜቱ መሞቱ ነው፡፡ ይህ ሰው ሥርዓት አልባ በመሆን ፊት ስሜቱን ቀጥሎ ሥጋውን መጨረሻም ነፍሱን ይገድላል፡፡ ለሰው ልጅም ህይወትን ያህል ጸጋ በአግባቡ መኖር ሳይችሉ እንደመቅረት ትልቅ ኪሣራ የለም፡፡ ንጉስ ዳዊት በቤተመንግስትም ሆነ በሌላ ስፍራ ያለው ነገር ሁሉ ዘላቂ የሆነ ደስታና የመንፈስ እርካታ ሊሠጠው እንደማይችል ተረድቶ ሲመረምር ነው፡፡በቤተ እግዚአብሔር መኖር የመጨሻው ምርጫው የሆነው፡፡
          የእግዚአብሔር ቤት የነፍስና የሥጋችን ፈጣሪ፣የስሜታችን ገዢ፣ ሳንጠይቀው የሚያስፈልገንን እውቆ የሚሠጠን አባት የጸጋው ማኅደር ናት፡፡በዚያ ለዘላለም የማይነጥፍ በዚያ በደም የለመለመ የማይደርቅ የፍቅር መስክ አለ፡፡ የማይጠፋ ተስፋ፣ የልብ ዕረፍት፣ የነፍስ መረጋጋት፣ የሥጋና የነፍስ ደኅንነት፣የስሜታችንና የመንፈሳችን ፈውስ፣የጭንቀታችን መራገፊያ ወደብ፣ዕንባችንን የሚያብስ መዳፍ በዚያ አለ፡፡
          በጥርጥር ለተመታን፣ በጭንቀት ለታመምን፣ በኑሮ ሸክም ለጎበጥን፣ ሰላም በማጣት ለታወክን፣ ደስታ ርቆን ለቆዘምን፣ ውሎ ለተምታታብን፣ መንገድ ጠፍቶን ለባዘንን ከህይወት ጋር ለተጣላን፣ ለመወሰን ለደከምን መፍትሔ በዚያ አለ በእግዚአብሔር ቤት፡፡
          ለዚህ ነው ንጉሡ ዳዊት "ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ" ያለው፡፡ ጨምሮም "በኃጥአን ድንኳን ከመቀመጥ የልቅ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥኩ" ብሏል፡፡ በኃጥአን ድንኳን ካለ ክብር በእግዚአብሔር ቤት ያለ ውርደት የተሻለ ነውና፡፡ በነውር ከመክበር ስለጽድቅ መዋረድ፣በኃጥአን ድንኳን ያሉ ነውሮች በእግዚአብሔር ቤት ቦታ የላቸዉም በእግዚአብሔር ቤት ጥርጥርና ክህደት የጠፋል፣ እምነትና ተስፋ ይሰፋል፣ ጠብ ክርክር ይደክማል፣ ፍቅር መተሳሰብ ይበረታል፣ ትዕቢት ይዋረዳል ትህትና ይከብራል ሀዘን ይከስማል፣ ደስታ ይናኛል፣ ርኩሰት አንገት ይደፋል፣ ንፅህና ይነግሳል፤ሞት ይሞታል ህይወት ይደምቃል የተሻለ ምርጫ የሆነውም ለዚህ ነው፡፡
          በክርስቶስ ወገኖቼ የሆናችሁ ሁሉ! ምኞታችን የተሻለ ምርጫችን የተስተካከለ እንዲሆን የሚያስተውል ልቦና የሚያገናዝብ ህሊና ተሰጥቶናል፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ በተለያቸው ዘንድ ምክራችን የማይጠቅም ቃላችንም ሞኝነት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለ ሞኝነት ከዓለም ጥበብ ይልቅ እንደሚጠበብ የሚያውቁበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ትሰማ ዘንድ ጆሮህ፣ ታይ ዘንደ ዓይንህ፣ ታስተውል ዘንደ አእምሮህ የተከፈተልህ አንተ ግን የደፍረት ዝናር ታጥቅ ዛሬውኑ ለመወሰንም ቁረጥ፡፡ ነገ አይሆንም ቅዱስ እግዚአብሔር ለኛ ያዘጋጀልን ዛሬን እንጂ ነገን አይደለም፡፡ ነገ ዲያቢሎስ ብዙዎችን ወጣት የገደለባት ሾተል ናት መርዛማ ሾተል፡፡
        ስለዚህ ወደ ያዕቆብ አምላክ ተራራ ወደ እግዚአብሔር ቤት በመሔድ ከአምላካችን ጋር እንገናኝ፡፡ ኃጢአትን ተፀይፈን ከርኩሰትም ነፅተን የቅዱስ መንፈሱ ማደሪያ መቅደስ ለመሆን እንጋደል፡፡የእግዚአብሔር ቤት እልፍ ነባብያን የሆኑ መቅደሶች የሚታነፁበት ስፍራ ነውና፡፡
መዝ 26፥4 ፣ መዝ 86፣ መዝ 121፥1 ፣ቆሮ 3፥17፣ ኢሳ 2፥1-6
ይቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ቀሲስ ታምራት ውቤ
ጥቅምት 2005 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment