በስመ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ
ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!
በቀደመ ጽሑፋችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ቻይ አምላክ
መሆኑን ድንቅ በሆነ ጽንሰቱ፣ ልደቱና በልጅነት ወራት አስደናቂ ህይወቱ ተመልክተናል፡፡ በይቀጥላል ጌታችን በእደ ዮሐንስ በፈለገ
ዮርዳኖስ ተጠምቆ ራሱን በትምርቱና በተዐምራቱ በገለጠበት ወቅት የህንኑ አስረግጧል፡፡
ዮሐ
2፥1-12 ፡- በተገለጠው ተዐምራት ጌታችን ውሃውን ወደ ወይን
መቀየሩን እናውቃለን፡፡ የውሃ እና የወይን ባህርይ በውስጣቸውም የሚይዙት ውሁድ(Substance)
የተለያየ እንደሆነ የተረዳ ነገር ነው፡፡ ጌታ በዚህ ተዐምራቱ ካልነበረ(ከሌለ) ነገር አንድን ነገር ማምጣት(መፍጠር) የሚችል መሆኑን
አሳይቶናል፡፡
ዮሐ 5፥1
፡- 38ዓመት ልምሾ ሆኖ እንደትኋን ካልጋ ተጣብቆ የኖረውን መፃጉዕ በቃሉ ብቻ መፈወሱ ሁሉን ቻይነቱን ያስረዳል፡፡
ዮሐ 9፥1
፡- በደረቅ ግንባር ላይ ዓይን መፍጠሩም እንደዚያው በዚሁ ምንባብ ላይ ዓይኑ የበራለት ሰው በሰጠው ምስክርነት "…ዓለም
ከተፈጠረ የዕውርን ዓይን የከፈተ ከቶ አልተሰማም" ማለቱ የጌታችንን ሁሉን ቻይነት
የሚያስገነዝብ ምስክርነት ነው፡፡
ማቴ 9፥27-31 ፡-
ባለው ተመሳሳይ ታሪክም ሁለቱ ማየት የተሳናቸው ሰዎች እነዲምራቸው ሲለምኑት "ይህን
ማድረግ እንድችል ታምናለችሁ?" ብሎ ነበር የጠየቃቸው ሁሉን
ማድረግ ከሚችል ከእርሱ በቀር በሥልጣን ይህን መናገር የሚችል ይኖራልን?
ሉቃ 13፥10-17 ፡-
18 ዓመት በድካም መንፈስ ጎብጣ የኖረች ሴት ሌሎችም በዚህ ጹሑፍ ያልተጠቀሱ ተዐምራቶች የሁሉን ቻይነቱ ማስረጃዎች ናቸው ወንጌል
ይህን በአንድ ቃል ሲያጠቀልለው "ህሙማንን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡለት
እርሱም ፈወሳቸው" ይላል ከመጣው ውስጥ ተስኖት ሳይፈውሰው የመለሰው አንድ ስንኳ የለም፡፡
በተፈጥሮ ላይ ሁሉን
ቻይነቱን ሲገልፅ
ሉቃ 5፥1-10 ፡- ስምዖን ጴጥሮስና ጓደኞቹ ዓሣ ማጥመድ ሌሊቱን
ሙሉ ሞክረው ተስኗቸው ቀርተዋል፡፡ ጌታ ወደ ታንኳይቱ ገብቶ መረባቸውን
በታንኳይቱ በስተቀኝ እንዲጥሉ ሲያዝ ሌሊቱን ደክመው መያዝ እንዳልቻሉ እንደቃሉ ግን መረቡን እንደሚጥሉ ገልፀው ቢጥሉ መረባቸው
እስኪቀደድ ዓሣ ማጥመድ ችለዋል ይህም በተፈጥሮ ላይ ያለውን ኃይል ያሳያል፡፡
ማቴ 8፥22-25 ፡- ሐዋርያት የሚቀዝፉትና ጌታ ከበስተኋላ ያንቀላፋባት ታንኳ በብርቱ ማዕበል ስትንገላታ
ባህሩም ሊደፍናት ሲቀርብ ሐዋርያት ጌታን ቀስቅሰው "ስንጠፋ አይገድህምን?" ባሉት ጊዜ ጌታ የእምነታቸውን ማነስ
ወቅሶ ነፋሱን እና ማዕበሉን ገሠፀ ታላቅ ጸጥታም ሆነ ሐዋርያትም ሁሉን ቻይነቱን በተረዱ ወቅት "ነፋሳትና ባህር ስንኳ
የሚታዘዙለት እርሱ ማንው? ብለው ሰገዱለት ይህም በተፈጥሮ ላይ ያለውን አዛዥነት በግልፅ ያስረዳል፡፡
ማቴ 14 ፡-በዚህ ሁለት ታላላቅ ተዐምራት ተደርገዋል፡፡ የመጀመርያው በአምስት ቂጣና በሁለት
ዓሣ አምስት ሺህ ያህል ወንዶች ሴቶችን ህፃናት ሳይቆጠሩ መግቦ 12 ቅርጫት ፍርፋሪ ማስነሳቱ ሲሆን ሁለተኛው ሐዋርያት በባህሩ
መካከል ሳሉ ባህሩን እነደየብስ እየረገጠ መምጣቱ፤ ጴጥሮስ ተጠራጥሮ ሊሰጥም ሲል በውሃ ላይ ቆሞ ውሃ ውስጥ የሚሰጥምን ማውጣቱ
ለሁሉን ቻይነቱ መጋለጫ አይደለምን?
እኒህ
ከላይ የተገለፁት ተዐምራት ሁሉ ከአእምሮ በላይ የሆኑ ቢሆኑም ለሰው ልጅ በተሰጠው ደካማ ቋንቋ ስለተፃፉ ግን ውጣቸውን በመንፈስ
ለመመርመርና ለማድነቅ ካልተዘጋጀን የሚፈጥሩብን ስሜትም እንዲሁ ደካማ ነው፡፡ በእምነት ለማደግ በቅዱስ እግዚአብሔር ፀጋ ለመበልፀግ
ለሚጋደሉ ግን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ዓለማትን የፈጠረና ሁሉ በእርሱ ትዕዛዝ የሚመራ መሆኑን ለመረዳት ታሪኮቹ ከበቂ በላይ
የሆኑ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ባነበብነው መልዕክት ጌታ መንፈስ ቅዱስ ህሊናችንን ለእውነታ ምርኮ ልቦናችንን ለፍፁም አምልኮ የተዘጋጀ እንዲሆን ይርዳን!
ይቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ቀሲስ ታምራት ውቤ
ጥቅምት 2005
No comments:
Post a Comment