Friday, April 12, 2013


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
"…ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፤ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና"ፊልጵ 5፥23
በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!
·   ስለ ዕለተ ሞትህ(ሽ) አስበህ(ሽ) ታውቃለህ? ለመሞትህ(ሽ) ምን ያህል እርግጠኛ ነህ(ሽ)?
·   በሞትህ ጊዜ ምን ዓይነት ሒደቶች ይጠብቁኛል ብለህ(ሽ) ታምናለህ?
·   ጌታ ክርስቶስን ከመናፈቅህ(ሽ) የተነሣ ሞትን ተመኝተህ(ሽ) ታውቃለህ?
·   በዚህች ቅጽበት ለመሔድ (ሞትን ለማስተናገድ) ዝግጁ ነህ(ሽ)? አዎን! ምክኒያት 
አይደለሁም- ምክኒያት

 
   የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ወደ አጠቃላይ ንባቡ ከመሔዳችሁ በፊት ከላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች መንፈሳችሁን ለራሳችሁና ለቅዱስ እግዚአብሔር ታማኝ በማድረግ በጹሑፍ መልስ ስጡ፡፡ በመልሳችሁ እርግጠኛ ስትሆኑ ቀሪውን ታነቡ ዘንድ ተፈቅዷል፤መታዘዝ በዚህ አለ!
   በመጽሐፍ ቅዱስ ከምናነባቸው አስደማሚ ነገሮች አንዱ ይኸው የቅዱሳን ናፍቆት ነው፡፡ በዚህ ከዚህ ዓለም የመለየት የቅዱስ ጳውሎስ ናፍቆት ሌሎችም ቅዱሳን ተባብረውበታል፡፡ ክቡር ዳዊት "ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፤አቤቱ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤መቼ እደርሳለሁ የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ?" በማለቱ ወንጌላዊው ዪሐንስም "ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና" በማለቱ ናፍቆታቸው ተገለጠ፡፡ ክርስቲያኖች ሆይ በእኒህ ቅዱሳን ውስጥ የነበረው "ሀሳብ" ወይም "ምኞት" አይደለም እንደ እሳት የሚበላ እንደ ውኃ ጥም የሚያቃጥል" ናፍቆት" እንጂ፡፡ መዝ 41(2)፥1-2፣ ራዕይ 22፥20
   በምድረ በዳ የሚሄድ ሰው ከውኃና ከእረፍት በቀር ምን ይናፍቃል? ልብስና ጌጥ ብርና ወርቅ ሌላውም ሁሉ በዚያ በርሃ ሸክም ቢሆን እንጂ ተስፋ አይሆንም፡፡ የዓለም ሀብት ቢሠፈር ጠብታ ውኃ የምትሠጠውን እርካታ የሚመዝን ዋጋ አይኖረውም፡፡ ከጽድቅ ምድረ በዳ በሆነች ዓለም ለሎሎች ብርሃን እንዲሆኑ ተወስኖባችው የዓለምን ርኩሰት ለማየትና ለመስማት ሳይፈልጉ በዚህ የተወሰነላቸውን ጊዜ እንዲኖሩ የተፈረደባቸው ቅዱሳን ነፍሳቸው የዓለምን ርኩስት በመፀየፍና ተወዳጁን ጌታቸውን በመናፈቅ ትጨነቃለች፡፡
የፍቅሩ ማዕበል የሚያማታት መዓዛ ቅድስናው የሚያውዳት ነፍሳቸው በሕያዋን ምድር ቅዱሱን ለማየት ትጠማለች ትናፍቅማለች፤ ቀን ዕረፍት ሌት እንቅልፍ አጥታ ትቃትታለች፡፡ የተጠማ የናፈቀ ለዓይኖቹ እንቅልፍ ለሽፋሽፍቶቹስ እረፍት እንዴት ይሠጣል?
ቅዱስ ጳውሎስ በህይወት መቆየቴ ለእናንተ ይጠቅማል ቢልም የእሱን ናፍቆት ግን ገልጿል፡፡ እውነት ነው የቅዱሳን በእግዚአብሔር ህዝብ መካከል መኖር የእውነተኛ ሐዋርያት ለመንጋው የሚራሩ እረኞች መኖር ለህዝቡ ጥቅም ነው፡፡ በምክራቸው ያፅናኑታል፣በቃላቸው ተስፋውን ከፍ ያደርጉታል፣ በተግሣጻቸው ከኃጢአት በንስሐ ወደ ጽድቅ የመልሱታል፣ በጸሎታቸው መዓትን ያርቁታል በረከትን ያቀርቡለታል ጉድለቱንም ይሞሉለታል፡፡
ሀሰተኞች እየተባሉ እኛን ወደእውነት መምራት፣እየተናቁ እኛን የታወቅን ማድረግ፣ እየተዋረዱ ክብርን ማሠጠት፣ ኃዘንተኞች ሆነው ለእኛ ደስታን መዝራት፤ በድህነት ኖረው ባለጠጎች ማድረግ፣ ሁሉን እያጡ ሁሉን ለእኛ ማሰጠት እየሞቱ የክርስቶስ ሕይወት በእኛ እንዲበራ መጋደል የቅዱሳን ተግባር ነው፡፡ ሰውን ወዳጅ ወደሆነው ጌታ አስክንቀርብና በፍጹም ህሊና ለመታዘዝ እከክንማረክ የመጨረሻውን ውርደት መቀበልና እንደ ዓለም ጥራጊ ጉድፍ ተደርገው መቆጠር የቅዱሳን ደስታቸው ነው፡፡1ቆር 4፥8-13፤ 2ቆሮ6፥4-10፤ዕብ11፥23-28
   ይህም ለእኛ ጥቀም እንጂ ለእነርሱ ምቾት አይደለም፡፡ ናፍቆታቸው ዕረፍታቸው ምቾታቸው ግን ሁሌም ከእርሱ ከከጌታቸው ጋር መኖር ነው፡፡ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ሞትን ይመኛሉ የከበረ ሲዋረድ፣ ያገኘ ሲያጣ፣ ያመነ ሲከዳ፣ ያፈቀረ ሲጠላ እንዲሁም በጽኑ ደዌ ሲያዝ፤ የሚወደውን በሞት ሲነጠቅ፣ ከገባበት አጣብቂኝ መውጫ ቀዳዳ አጥቶ ተስፋ ሲያጣ፣ ዙርያው ገደል ሲሆንበት ሞትን ይመኛል፡፡ ግልግል ነው ብሎም ያስባል፡፡ በእርግጥም ከሆነ???
   የቅዱስ ጳውሎስና የሌሎችም ቅዱሳን ከዚህ ዓለም መሰናበትን መናፈቅ ግን ከዚህ እጅግ ይለያል፡፡ በምድራዊ የኑሮው ምቾት አንፃር ካየነው ክቡር ዳዊት እንደ ንጉሥነቱ ሁሉ የተረፈው ነው፡፡ ቅ.ጳውሎስም ለኑሮው በእጁ ደክሞ ለመጠቀም የሚያንስ ሰው አልነበረም፡፡ ደግሞስ ሁሉን ትተው የተከተሉ በፈቃዳቸው አልነበረምን? "…ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት አኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት…" ሲል ለዓለም ምኞት ለሥጋ አምሮት ምውት መሆኑን መግለፁ አይደለምን፡፡
ሐዋርያቱ በዓለም ያወጁት ዓዋጅ "ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል መሆኑን ዓለምንና በዓለም ያለውን መውደድ ከፍቅረ እግዚአብሔር እንደሚለይ ዓለሙና ምኞቱ ኃላፊ ጠፊ መሆናቸውንና ፈቃደ እግዚአብሔርን የሚፈጽም ግን ለዘላለም እንደሚኖር አልነበረምን? 1ዮሐ 1፥15-17፣ያዕ 4፥4፤ ገላ 6፥14፤ ዕብ11፥35-38
    ስለዚህ ቅዱሳኑ ከዚህ ዓለም መሔድ የተሻለ እንደሆነ የገለፁት በዚህ ምድር ኑሮ ስላስመረራቸው አግኝተው ስላጡ ከብረው ስለተዋረዱ አይደልም፡፡ " አንዳች የሌለን ስነመስል ሁሉ የእኛ ነው" ማለታቸውን አስታውስ፡፡ ከዚያም በተጨማሪ በምድራዊ ሀብትና ሥልጣን ጥበብና የዘር ግንድ የማይገኝ ታለቅ ሀብት እንደነበራቸው የታወቀ የተረዳ ነገር ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ ዓለም መለየትን ለምን ናፈቁ?
፩. ዓለምን መጥላታቸው ነው፡፡ ዓለምን መጥላት ማለት ቅዱስ እግዚአብሔር ለምግበ ሥጋና ለአንክሮ ለተዘክሮ የፈጠራቸውን ፍትረታቱን እና በውስጣቸው ያለውን ተፈጥራዊ ጸጋ አንዲሁም ነዋሪዎቿን መጥላት አይደለም፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ከመፍጠር ያልናቀውን እንወድ ዘንድ የተገባ ነውና፡፡
የምንጠላው የምንፀየፈው ርኩሰቷን ግልሙትናዋን ክፋቷን ወዘተ…ነው፡፡ ቅዱሳን መቼም ቢሆን ንፅህናቸው ከርኩሰቷ፤ቅድስናቸው ከግልሙትናዋ፣ የዋሃታቸው ከክፋቷ፣ እውነታቸው ከሀሰቷ፣ ርህራሄያቸው ከጭካኔዋ ጋር ሊስማማ አይችልም፡፡ ታለቁ በታናሹ ብርቱው በድካማው ላይ የሚሠራውን ግፍ መመልከት፤ ከህይወት መንገድ ስተው የሚጠፉትን ማየት፤ በሰነፎችና በኃጢአተኞች አፍ በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሚነገረውን ስድብ መስማት ለቅዱሳን ታላቅ ስቃይ ነው፡፡ ከዚህ ሁለ የሚያርፉት ጽድቅና ቅድስና በነገሠባት ሀሰትና ክፋት በማይሠለጥንባት በዚያች የቅዱስ እግዚአብሔር ከተማ መሆኑን ያውቃሉና መሰናበታቸውን ይናፍቁታል፡፡
፪. ከደካማው ባህርይ መላቀቅን መናፈቃቸው ቅዱሳን ምንም እንኳ በጸጋ እያደጉ በሔዱ ቁጥር ፈቃደ ሥጋቸው ለፈቃደ ነፍሳቸው ቢገዛም፤ እነርሱም ከቅድሰናቸው የተነሣ በአካለ ሥጋ እያሉ ለነፅሮተ ሥሉስ ቅዱስ እስከመድረስ ቢበቁም እንኳ ያለተከፍሎ በእያንዳንዷ የጊዜ ሽርፍራፊ ሁሉ ከተወዳጁ ጌታ ጋር ለመሆን ካላቸው ናፍቆት የተነሣ ማነቆ ከሆነባቸው ምድራዊ ቆይታ መሰናበትን ይሻሉ፡፡ ለቅዱሳን የሚበሉባትና የሚጠጡባት የሚያርፉባትና የሚያንቀላፉባት ሰዓት ሁሉ ፀፀት ናት፡፡ ናፍቆታቸው መብልና መጠጣቸው እረፍታቸውም እደመላእክት እርሱ ጌታቸው እንዲሆን ነውና፡፡ ይህ ደግሞ በአፀደ ነፍስ እንጂ በአፀደ ሥጋ አይሆንም፡፡ ሰው ወደሌለበት ጥልቅ በረሃ መመነናቸው ቅሉ ለዚሁ ነው፡፡ ከዚህ ዓለም የሚሆን ፍልሰታቸውንም መናፈቃቸው ምክንያቱ ይሄው ነው፡፡
  ተወዳጆች ሆይ ቅዱሳን የልባቸው ናፍቆት የነፍሳቸው ጥማት ከሆነው ጌታ ጋር ለመኖርና ህብረት ለማድረግ የዚህን ዓለም ህይወት ረብ እንደሌለው ነገር ቆጠሩት፡፡ ሁሉን ትተው በህይወታቸው ሳይቀር ጨክነው ተከተሉት፡፡ "ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ፡፡" እያሉ ስለ ክርስቶስ ፍቅር ወደ ሞት በፈገግታ ሔዱ፡፡ ሮሜ 8፥18
እኛ ለወደደን እስከሞትም ራሱን አሳልፎ ለሰጠልን ለእርሱ ኃጢአትን፣ ክፋትን፣ ቂምን፣ ረብ የለሽ ደስታን መተው አለመቻላችን ምን ያህል ደካማነት ነው፡፡
ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የመኖርን ደስታ በቅድስና በመኖር የቀመሱት እነርሱ ከዚህ ዓለም ተለይተው ለዘላለም በማይነጥፍ ደስታ ውሰጥ ለመኖር ናፈቁ፡፡
መቼ እንደምንጠራ የሚያውቀውና ሰዓቲቱን የሚወስነው ጠሪያችን ብቻ ነው፡፡ እርሱ ደግሞ የነፍሳችንና የሥጋችን የጊዜያዊውና የዘላለማዊው ዓለም ገዢ ነው፡፡ ከዙፋኑ ፍትህ ከቃሉም እውነተኛ ፍርድ ይወጣል፡፡ ፍርዱንም ይለውጥ ዘንድ የሚችል ከቶም የለም፡፡
የተሻለውን መምረጥ በዚህ አለ፡፡ በጊዜያዊው ለዘላለማዊው በምድራዊው ለሰማያዊው መዘጋጀት፡፡ ክርስቶስን በመመምሰል ቆይቶ ለዘላለም ከእርሱ ጋር ለመኖር መሔድ ወይም…
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር
የካቲት 2005


Wednesday, April 10, 2013

የተሻለ ምርጫ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
    በተለያየ አህጉር አንድ ጊዜ ስለተሠጠች የቅዱሳን ሃይማኖት እየተጋደላችሁ፤ ዲያብሎስንና ሥራውን ሁሉ በእምነት ኃይል እየተቃወማችሁ የጌታችንን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም መምጣት በተስፋ ለምትጠባበቁ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!
   ባለፉት ጊዜያቶች በላክሁላችሁ ጦማሮች ቅዱስ እግዚአብሔርን በመከተልና፤በቅድስና ስፍራው በቤቱ በመገኘት የምናገኘውን መልካም ነገርና፤ ምርጫችንም ምን መሆን እንዳለበት ተነጋግረናል፡፡ ለዛሬ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በገለጠልን መጠን ሌላ ሦስተኛ ጠቃሚ ነጥብ አናያለን፡፡
ከብዙ ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ(ቃል) ይሻለኛል መዝ118፥70
   ነብዩ ዳዊት በዚህ የመዝሙር ቃሉ ሁለት በሰው ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት የሚስቡ (የሚወደዱ) እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን አነፃጽሯል፡፡ አንዱ ጊዜያዊ ሌላው ዘላለማዊ፣ አንዱ ምድራዊ ሁለተኛው ሰማያዊ፣ ላንደኛው ከተገዛን ወደ ጥፋት የሚወስደን ሁለተኛው ግን ከጠበቅነው የሚጠብቀን ዘላለማዊ ክብርንም የምናገኝበት ነው፡፡ አስቀድመን የመጀመርያውን እንይ፡-
ብርና ወርቅ፡- በዓለማችን ስለ ብርና ወርቅ ተብሎ የሰው ልጅ የሆነውንና ያደረገውን ከመናገር ያልሆነውንና ያላደረገውን መናገር ይቀላል፡፡ የሚነገር ከተገኘ፡፡ ብዙ ሀገር ፈርሷል፤በርካታ ህዝብ ለባርነት ፈልሷል፤ለነፃነትና ለክብር ሳይሆን ለወርቅና ለብር ሲባል ብዙ ጦርነት ተካሂዷል ብዙ ንፁህ ደም ፈሷል፡፡ ከቤተመንግስት እስከ ቤተክህነት፣ ከንጉሰ እስከ ጳጳስ ፣ ከግል እስከ

ቡድን ተንኮል ገምዷል ሴራ ሸርቧል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ልጆች ወላጆቻቸውን፣ ባለትዳሮች የፍቅር የኑሮ አጋሮቻቸውን ከድተዋል ለሞትም ዳርገዋል፡፡ በዘመናችንም ብዙ ይደረጋል፡፡
 በአጠቃላይ የቀን ቅዥታችን የሌሊት ህልማችን ዕለት ተዕለት የምንባክነው ብርና ወርቅ ለማግኘት ነው፡፡ በዚህ ዘመን ለብርና ለወርቅ ክብሩን ያልጣለ ማግኘት ይቸግራል፡፡ሴቶችና ወንዶች ለገንዘብ ክቡር ሰውነታቸውን ለዝሙት ሽጠዋል፡፡ እንኳን ሌላው ራሳቸው የሆኑትንና የሚፈፀምባቸውን ለመግለፅ እስኪቀፋቸው ተዋርደዋል፡፡ ህፃናት በመጫወቻ ዕድሜያቸው በሴሰኝነት ራሳቸውን በሳቱ ባለፀጋዎችና በገንዘብ ላበዱ ጨካኞች መጫወቻ ሆነዋል፡፡ ገንዘብ እንዲሞላ ሀብት እንዲሠምር ሰዎች እንደከብት ታርደው መሥዋዕት ሆነዋል፤ደማቸውም ለዲያቢሎስ ግብር ቀርቧል፡፡ የሚብሰውም ሰው በምድር በሰማይ የሚከብርበትን ከፈጣሪው ጋር አንድ የሚሆንበትን ሃይማኖቱን ሳይቀር በብርና ወርቅ ለውጧል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም "ገንዘብ በመመኘት ይረቡባችኋል" ቅዱስ ጳውሎስም "…ዳሩ ግን ባለጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ፤ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ፡፡ ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፤አንዳነዶችም ይህን ሲመኙ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ፡፡" ብለዋል፡፡ስለ ብርና ወርቅ ይህቺ ዓለም ምንያህል ርኲሰትን ተሸከመች፤ ፈጣሪስ የቱን ያህል ታገሠን፡፡ 2ጴጥ 2፥3፤1ጢሞ 6፥6-10
   ጌታም አስቀድሞ "ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል ወይም ወደአንዱ ይጠጋል፤ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም" ሲል አስጠንቅቆናል፡፡ ማቴ 6፥24
 
   እንዲህም ሆኖ ብርና ወርቅ እርካታን ሰጥቶን፣ ከደዌ ፈውሶን፣ ሰላምን አስገኝቶልን እውነተኛ ወዳጆችን አቅርቦልን፣ ይልቁንም ከሞት አድኖን ከእግዚአብሔር ቁጣም አስጥሎን አያውቅም፡፡ ይልቁንም በተቃራኒው ነው፡፡ " ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧል…ያ ቀን! የመዓት ቀን፣ የመከራና የጭንቀት ቀን ፣ የመፍረስና የመጥፋት ቀን ፣ የጨለማና የጭጋግ ቀን ፣ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ፣ በተመሽጉ ከተሞችና በረዘሙ ግንቦች ላይ የመለከትና የሰልፍ ጩኸት ቀን ነው፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርተዋልና ሰዎችን አስጨንቃለሁ፤እንደ ዕውርም ይሄዳሉ፤ ደማቸውም እንደ ትቢያ፤ ሥጋቸውም እንደ ጉድፍ ይፈስሳል፡፡ በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ብራቸውንና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም…" ትን.ሶፎ 1፥14-18
   እንግዲህ ብዙ የምንሆንለትና የምናደርግበት ብርና ወርቅ ኃይሉና ጉልበቱ እዚህ ድረስ ነው፡፡ አንባቢው ያስተውል በደዌ የሚማቅቁ በሰላም እጦት የሚሳቀቁ በሞትና በእግዚአብሔር ፍርድ ሳያስቡት ድንገት የታነቁ ብዙ ባለፀጋዎች ከእኛ በፊት አልፈዋል፡፡ በጊዜው ካልነቃን በእኛም የሚደርስ ይኸው ነው፡፡ የሰው ሕይወቱ በገንዘቡ ብዛት አይደለምና፡፡ ሰው ዓለሙን ቢያተርፍ ነፍሱን ካጣ ምን ይጠቅመዋል፤ ስለ ነፍሱስ ምን ቤዛ ይሠጣል? ሉቃ 12፥13-21፣ማቴ 16፥26-27
በአንፃሩም በተሠጠን ገንዘብ መልካም ብንሠራበት ከእግዚአብሔር ዘንድ መልካም የሚሆንልን አይደለምን? ጌታም "… የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሏችሁ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ" ሲል መክሮናል ፈፅመው የተጠቀሙበትም ብዙዎች ናቸው፡፡

የእግዚአብሔር ሕግ(ቃል)፡- የሰው ልጅ ቅድሚያ ለያስተውለው የሚገባው ዋና ነገር ቢኖር ጌታ "ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም" ብሎ ያስተላለፈው ታላቅ መልእክት ነው፡፡ መብላት መጠጣትና መራባት ሕገ እንስሳ እንጂ ሕገ ሰብእ አይደለም፡፡ ሰው ከመብላት ከመጠጣትና ከመራባት ያለፈ ዓላማ ይዞ የተፈጠረ ፍጥረት ነው፡፡ ይኸውም ዓላማ የፈጣሪውን ክብር መውረስ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በእግዚአብሔር ቃል(ሕግ) መሠላልነት የሚደርስበት ሠገነት ነው፡፡ ለሰው የእግዚአብሔር ቃል ከሥጋና ከነፍስ ደዌ የሚፈወስበት መድኃኒት፤ከሥጋዊም ሆነ ከመንፈሳዊ የጠላት ሠራዊት የሚሸሽግበት ዐለት፣ ከርኲሰቱ የሚጠራበት፣ ከድካሙ የሚበረታበት፣ ከስብራቱ የሚጠገንበት፣ከሀዘኑ የሚፅናናበት፣ከድንቁርና ጨለማ ነፃ የሚሆንበት ብርሃን ነው፡፡ ሥጋ የሚያስፈልገውን ካጣ ከስቶ  ጠውልጎ ውበቱ ደምግባቱ ተበላሽቶ እንዲታይ ነፍስም የእግዚአብሔር ቃል ከተለያት ውበት ደም ግባቷ የሆነ ንፅህና ቅድስና ጠፍቶባት ጠውልጋ ተበላሽታ ትታያለች፡፡ የሥጋ ክሳትና ጉስቁልና በዓይነ ሥጋ እንደሚታይ የነፍስ ጉስቁልና በዓይነ ልቡና ይታያል፡፡ ሰው በዝሙት፣ በሀሰት፣ በስርቆት፣በክፋት፣ በሀሜት፣በስድብ እግዚአብሔርን ባለመፍራት ሰውንም ባለማፈር ሲመላለስ እንኳን በሕገ እግዚአብሔር ፀንተው ላሉ፣ በግብር ለሚመሰሉትም ይከፋል፡፡ በሁሉም ይነወራል፡፡ የነፍስም ጉስቁልና በዚህ ይታወቃል፡፡
ለዚህ ነው ነብዩ ዳዊት " ሕጉን በቀንና በሌሊት የሚያስብ ሰው ቅጠሉ እንደማይረግፍ ፍሬዋንም በየጊዜዋ እንደምትሠጥ በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደተተከለች ዛፍ ነው" ያለው፡፡ እስኪ ለጥቂት ደቂቃ ኑሮአችንን ያለ ውኃ ለማሰብ እንሞክር፡፡ ውኃን ብናጣ ምን ሊፈጠር ይችላል? ያለውኃ ምግባችንን ማብሰል እንዳንችል፤ ያለ ቃለ እግዚአብሔርም  እርሱን ወደማወቅ ብስለት ልንደርስ አንችልም፡፡ ያለውኃ የሥጋ ንፅህናን ማግኘት እንዳንችል፤ ያለ ቃለ እግዚአብሔርም የነፍስ ንፅህና አይገኝም፡፡ ያለውኃ ቤት መስራት እንዳይቻል ያለ ቃለ እግዚአብሔርም ሰማያዊ ቤት አይኖረንም፡፡ ያለውኃ በሥጋ መኖር እንዳይቻል ያለቃለ እግዚአብሔርም ነፍስ ሕይወት የላትም፡፡ ሐዋርያት ለዚህ ነው ጌታችንን" ካንተ ወዴት እንሔዳለን አንተ የህይወት ቃል አለህ" ያሉት፡፡
   ነብዩ ዳዊት ለክብረ መንግስቱ የሚገበርለት ብዙ ብርና ወርቅ ቢኖርም ሕይወት እንደማይሆነው ከሞትም እንደማያድነው ሰለተገነዘበ ነው ሕግህ(ቃልህ) ይሻለኛል ያለው፡፡ ሰው በብር በወርቅ ከሚያጌጥ በእግዚአብሔር ሕግ ቢያጌጥ፤ በብር በወርቅ ከሚከብር በእግዚአብሔር ቃል ቢከብር ለሰውም ለእግዚአብሔርም ደስ ያሰኛል፡፡ ብዙ የምድር ባለፀጋዎች አልፈዋል ከነስም አጠራራቸውም ተረስተዋል፡፡ በእግዚአብሔር ቃል የከበሩ ግን በምድርም ሆነ በሰማያት የዘላለም መታሰቢያ ቆሞላቸዋል፡፡
-ዳዊት እንደልቤ የተባለ ስለሀብቱ ብዛት ሳይሆን እግዚአብሔርን ሰለመፍራቱና ቃሉን ስለማፍቀሩ ነው፡፡                                       -ነቢያትና ሐዋርያት ጻድቃንና ሰማዕታት የሚታወሱት በባለሟልነትም የሚታሰቡት ሕጉን ሰለጠበቁና ቃሉን ሰላገለገሉ እንጂ ስለ ብርና ወርቃቸው ብዛት አይደለም፡፡ ኢሳ 56፥1-ፍፃሜ
-ሙሴም ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት እስኪነጋገር ድረስ በባለሟልነት የከበረ የግብፅን ገንዘብና ሹመት ስለመናቁ አይደለምን? ዕብ11፥23-28
   በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አብራችሁኝ የተስፋው ቃል ተካፋዮች የሆናችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ ቃሉ በእኛ ቢኖር እኛም በቃሉ እንኖራለን፡፡ በትዕዛዙ የምንሔድ በቃሉም የምንኖር ከሆነ ራሱን ይገልጥልናል ይወደናልም በእኛ ዘንድም መኖርያውን ያደርጋል፡፡ ዮሐ14፥18-24
ቃሉን የማይናፍቅ ሕጉን ሲሰማ የሚሰለቸው ራሱ በፈጠረው በሚመቸው ህግ ለሚኖር ለዚያ ሰው ወዮለት፡፡ ታላቅ ፍርድ ይጠብቀዋልና፡፡ ሞት በሙስና አይታማም፡፡መማለጃም ሰጥቶትም ህይወቱን ያረዘመ ሰው ዓለም ከተፈጠረ አልሰማንም፡፡ የልዑሉን ትዕዛዝ ፍርዱንም የሚያስፈፅመው መላዕክትም በብርና በወርቅ አይደለሉም፡፡ በሲዖልም በሀብታችን የተሻለ ቦታን ልንመርጥ አይቻለንም፡፡ ያ ዓለም ብርና ወርቅ የሚሠለጥንበት ዓለም አይደለምና፡፡
ቃሉን የሚያፈቅሩ ሕጉንም የሚወዱ ግን ዝማሬያቸው ይህ ነው፡፡
ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል አቤቱ ሕግህን እንደምን እጅግ ወደድሁ ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው፡፡ ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፈጭ ነው ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው፡፡ መዝ 118፥1-ፍፃሜ
ስለዚህ ቃሉን የያዙ በሕጉም የሚኖሩ ግን በድል ይወጣሉ፡፡ የሲዖል ግርማም በእነርሱ ላይ ኃይል የለውም፡፡ በጽዮን ተራራ ከበጉ ጋር መኖር ዕድል ፈንታቸው ነው፡፡ እርሱ አምላካቸው እነርሱ ሕዝቦቹ ይሆናሉ፡፡ ረሃብና ጥም ፣ ደዌም ፣ጉስቁልናም፣ መገፋትና መበደልም ያቀን ሀሩርና የሌሊት ቁር አያስጨንቃቸውም፡፡ ያለፈውን ሥርዓት አሳልፎ እንደ ተስፋ ቃሉ ሁሉን አዲስ ያደርጋልና፡፡ እንደ ተስፋ ቃሉ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር መጠበቅ ወይም ለኃላፊ ብርና ወርቅ መተናነቅ ምርጫው የራሳችን ነው፡፡ የተሻለውን ለመምረጥ ህሊና ተሰጥቶናልና፡፡ ራዕይ 7፥13-17፣ 2ጴጥ 3፥13
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ቀሲስ ታምራት ውቤ

የተሻለ ምርጫ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
         በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!
እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ መዝ 26፥4
           እስትንፋሰ እግዚአብሔር የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ "የተሻለ ምርጫ" ብሎ ከሚያስቀምጣቸው አንዱ ከላይ የተመለከትነው እፁብ ድንቅ ምርጫ ነው፡፡ ንጉስ ዳዊት በቤተ እግዚአብሔር መኖር በቤተመንግስት ከመኖር ወይም ሌላ ሥፍራ ከመገኘት የተለየ ነገር እንዳለው ተሰምቶታል አውቋልም፡፡
          ብዙ ጊዜ እንስሳዊ የሆነ ባህርያችን ተድላ ሥጋ የሚደረግባቸውን ቦታዎች ይመርጣል፡፡ ብዙ መብልና መጠጥ ያለበት፣ ጨዋታና ሣቅ የነገሠበት ወይም ዕረፍተ ሥጋ(የሥጋ ምቾት) የተሟላበትን ቦታ ይመኛል ይስማማዋልም፡፡ከዚያ የከፋው ደግሞ በጤናማ አእምሮ የማይደረጉና ጊዜያዊ ለፍትወተ ሥጋ እርካታን የሚሠጡ ዲያቢሎስ በቅዱስ እግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን የልጅነት የክብር አክሊል የተደፋለትን የእግዚአብሔር መንፈስ መቅደስ የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ አካል የተባለን የሰው ልጅ የመጨረሻውን ውርደት ለማዋረድ ያዘጋጃቸውን በመዝናኛና ከጭንቀት መገላገያ በሚል ስም የተፈጠሩ ወጥመዶች፡- መጠጥ፣ አደንዛዥ ዕፆች፣ የተፈጥሮን ክብርና ውበት የሚያጎድፍ ድርጊቶች ወዘተ… የሚዘወተሩባቸው ሥፍራዎች መገኘት የሚወዱ በርካታቶች አሉ፡፡ ይህም ውጤቱ ለሥጋ ውድቀት ለነፍስም ውርደት ነው፡፡
         ሥፍራዎቹም ሆኑ የሚፈፀምባቸው ነውር የምንፈልገውን ደስታ አይሠጡንም ይልቁንም ይበልጥ የልማዳችን ባርያ እየሆንን ባዶነታችን እየሰፋ ተስፋ መቁረጣችን እየበረታ ይሔድና ለደስታ ብለን የጀመርነው ህይወት ለመከራ ይዳርገናል፡፡ የተሻለ ምርጫ አለመሆኑን የምንረዳው ምርጫችንን ለማስተካከል አቅማችንም ዕድላችንም ከተሟጠጠ በኋላ ነው፡፡
        በጥንቃቄ ያልተያዘ ምግብ እንደሚበላሽ ጣዕምና መዓዛው እንደሚቀይር ሁሉ በተፈጥሮ የተሠጡንን ስሜቶቻችንን በጥንቃቄ ካላስተናገድናቸው ይበላሻሉ፡፡በትክክል ሊሠጡን የሚገባቸውን እርካታ መስጠት ይሳናቸዋል፡፡ለህይወታችን ቅመም የሆኑት ስሜቶቻችንም ይሞታሉ፡፡ለዚህ ምክኒያቱም "ሁሉ በሥርዓትና በአግባብ ይሁን!" ተብለን የተመከርነውን አለመፈፀማችን ነው፡፡
        በዚህ ዓለም ደስታን ሊሠጡ ይችላሉ ተብሎ የሚታሰቡ ነገሮች በቀላሉ ማግኘት የሚችሉ ሰዎች ተስፋ ቢስ ህይወት ሲመሩ ብሎም ራሳቸውን ሲያጠፉ ሊደንቀን ይችላል፡፡ ምን ነካው? ምን ጎደለበት? ብለን እናስባለን ምክንያቱ ከሥጋው በፊት ስሜቱ መሞቱ ነው፡፡ ይህ ሰው ሥርዓት አልባ በመሆን ፊት ስሜቱን ቀጥሎ ሥጋውን መጨረሻም ነፍሱን ይገድላል፡፡ ለሰው ልጅም ህይወትን ያህል ጸጋ በአግባቡ መኖር ሳይችሉ እንደመቅረት ትልቅ ኪሣራ የለም፡፡ ንጉስ ዳዊት በቤተመንግስትም ሆነ በሌላ ስፍራ ያለው ነገር ሁሉ ዘላቂ የሆነ ደስታና የመንፈስ እርካታ ሊሠጠው እንደማይችል ተረድቶ ሲመረምር ነው፡፡በቤተ እግዚአብሔር መኖር የመጨሻው ምርጫው የሆነው፡፡
          የእግዚአብሔር ቤት የነፍስና የሥጋችን ፈጣሪ፣የስሜታችን ገዢ፣ ሳንጠይቀው የሚያስፈልገንን እውቆ የሚሠጠን አባት የጸጋው ማኅደር ናት፡፡በዚያ ለዘላለም የማይነጥፍ በዚያ በደም የለመለመ የማይደርቅ የፍቅር መስክ አለ፡፡ የማይጠፋ ተስፋ፣ የልብ ዕረፍት፣ የነፍስ መረጋጋት፣ የሥጋና የነፍስ ደኅንነት፣የስሜታችንና የመንፈሳችን ፈውስ፣የጭንቀታችን መራገፊያ ወደብ፣ዕንባችንን የሚያብስ መዳፍ በዚያ አለ፡፡
          በጥርጥር ለተመታን፣ በጭንቀት ለታመምን፣ በኑሮ ሸክም ለጎበጥን፣ ሰላም በማጣት ለታወክን፣ ደስታ ርቆን ለቆዘምን፣ ውሎ ለተምታታብን፣ መንገድ ጠፍቶን ለባዘንን ከህይወት ጋር ለተጣላን፣ ለመወሰን ለደከምን መፍትሔ በዚያ አለ በእግዚአብሔር ቤት፡፡
          ለዚህ ነው ንጉሡ ዳዊት "ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ" ያለው፡፡ ጨምሮም "በኃጥአን ድንኳን ከመቀመጥ የልቅ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥኩ" ብሏል፡፡ በኃጥአን ድንኳን ካለ ክብር በእግዚአብሔር ቤት ያለ ውርደት የተሻለ ነውና፡፡ በነውር ከመክበር ስለጽድቅ መዋረድ፣በኃጥአን ድንኳን ያሉ ነውሮች በእግዚአብሔር ቤት ቦታ የላቸዉም በእግዚአብሔር ቤት ጥርጥርና ክህደት የጠፋል፣ እምነትና ተስፋ ይሰፋል፣ ጠብ ክርክር ይደክማል፣ ፍቅር መተሳሰብ ይበረታል፣ ትዕቢት ይዋረዳል ትህትና ይከብራል ሀዘን ይከስማል፣ ደስታ ይናኛል፣ ርኩሰት አንገት ይደፋል፣ ንፅህና ይነግሳል፤ሞት ይሞታል ህይወት ይደምቃል የተሻለ ምርጫ የሆነውም ለዚህ ነው፡፡
          በክርስቶስ ወገኖቼ የሆናችሁ ሁሉ! ምኞታችን የተሻለ ምርጫችን የተስተካከለ እንዲሆን የሚያስተውል ልቦና የሚያገናዝብ ህሊና ተሰጥቶናል፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ በተለያቸው ዘንድ ምክራችን የማይጠቅም ቃላችንም ሞኝነት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለ ሞኝነት ከዓለም ጥበብ ይልቅ እንደሚጠበብ የሚያውቁበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ትሰማ ዘንድ ጆሮህ፣ ታይ ዘንደ ዓይንህ፣ ታስተውል ዘንደ አእምሮህ የተከፈተልህ አንተ ግን የደፍረት ዝናር ታጥቅ ዛሬውኑ ለመወሰንም ቁረጥ፡፡ ነገ አይሆንም ቅዱስ እግዚአብሔር ለኛ ያዘጋጀልን ዛሬን እንጂ ነገን አይደለም፡፡ ነገ ዲያቢሎስ ብዙዎችን ወጣት የገደለባት ሾተል ናት መርዛማ ሾተል፡፡
        ስለዚህ ወደ ያዕቆብ አምላክ ተራራ ወደ እግዚአብሔር ቤት በመሔድ ከአምላካችን ጋር እንገናኝ፡፡ ኃጢአትን ተፀይፈን ከርኩሰትም ነፅተን የቅዱስ መንፈሱ ማደሪያ መቅደስ ለመሆን እንጋደል፡፡የእግዚአብሔር ቤት እልፍ ነባብያን የሆኑ መቅደሶች የሚታነፁበት ስፍራ ነውና፡፡
መዝ 26፥4 ፣ መዝ 86፣ መዝ 121፥1 ፣ቆሮ 3፥17፣ ኢሳ 2፥1-6
ይቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ቀሲስ ታምራት ውቤ
ጥቅምት 2005 ዓ.ም

Monday, April 8, 2013

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (7)


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
መግቢያ፡ በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!
ሌላው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነቱን ከገለፀባቸው ባህርያት አንዱ ኃጢአትን የማስተሰረይ(ይቅር የማለት) ሥልጣኑ ነው፡፡
በመጽሐፍ እንደተፃፈ ኃጢአትን ማስተሰረይ ብቸኛ የቅዱስ እግዚአብሔር ሥልጣን ነው፡፡ በማር.ወን 2፥ 5፡- ላይ ሽባውን ሰው እንዲፈውስላቸው በአልጋ አድርገውና የቤቱን ክዳን ነቅለው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ሲያቀርቡት አንተ ሰው ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ነበር ያለው፡፡ በዚያ የነበሩ አይሁድም "ይህ ሰው በርግጥ ይሳደባል ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ማን ይችላል?" በማለት ሲያጉረመርሙ ጌታችን ግን "የሰው ልጅ ኃጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ሥልጣን እንዳለው እንዲያውቁ አስረግጦ ነግሯቸዋል፡፡ ሽባውንም ፈውሶታል፡፡ እዚህ ላይ"የሰው ልጅ" እያለ ጌታ የሚጠራው ራሱን እንደሆነ አስተውል፡፡
ኃጢአት የሚሠራ ሰው በዋናነት የሚበድለው ቅዱስ እግዚአብሔርን ነው፡፡ ምክንያቱም፡
1. ሕጉን ይተላለፋል አድርግ የተባለውን ሲያስቀር አታድርግ የተባለውንም ሲያደርግ የአግዚአብሔርን ሕግ ማቃለሉ አይደለምን?፡፡ ለልዑል እግዚአብሔር ፍቅርና ክብር እንዳለን የሚታወቅበት ብቸኛ መንገድ በቃሉ(በሕጉ) ታዛዥ ሆነን መገኘት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ዓመፀኞች ነን፤ ዓመፃ ደግሞ ኃጢአት ነው፡፡ ኃጢአትንም የሚያደርግ ከእግዚአብሔር አልተወለደም፤እግዚአብሔርንም አያውቀውም፡፡ 1ዮሐ 2
2. እግዚአብሔርን የሚበድለው የፈጠረውን ፍጥረት በማሳዘኑ ነው፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር የፍጡራኑ በደልና ሥቃይ የሚሰማው አምላክ ነው፡፡ ገዢያችን አባታችን ነውና፡፡ የግዛቱ መደፈርና የህዝቡ በጦርም ሆነ በምርኮ መንገላታት ንጉስን ከዙፋኑ አውርዶ ከቤተመንግስቱ አስወጥቶ ጦርነት እንደሚያስከትተው፤የሚስቱ የልጆቹ መጠቃት የአባትን ቁጣ ቀስቅሶ ለበቀል አንደሚያነሣሣው ለልዑል እግዚአብሔርም የፍጡራኑ መበደል አንዲሁ ነው፡፡ ከዚያም በላይ ከአካላችን አንዱ ብልት ላይ የሚደርስ አደጋ ህማሙ ነፍሳችን እንደሚሠማት ለጌታ እግዚአብሔርም በፍጡራኑ ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዲሁ ነው፡፡
በመሆኑም ሰው ኃጢአት ሠርቶ ባልንጀራውን ቢበድል ይቅርታን ማግኘት ያለበት ከተበዳዩ ብቻ ሳይሆን በዋናነት ከልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ ምሳሌ፡- አንድ ሰው ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች ብላቴናን በግዳጅ ቢደርስባት ጥቃቱ(በደሉ) የእርሷ ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ፣ የማኅበረሰቡና የመንግስት ጭምር ነው፡፡ ምንም እንኳ በዳዩ ሽማግሌ ልኮ ካሣ ከፍሎ ከተበዳይዋም ሆነ ከቤተሰቧ ይቅርታን ቢያገኝ የሀገሪቱን ሕግ በመተላለፉና በአንዲት ንፁህ ዜጋ ላይ ወንጀል በመፈፀሙ በመንግስት ሕግ ከመጠየቅ አይድንም፡፡ ማኅበረሰቡም ይህ ሰው ነገ ሊያደርሰው የሚችለው ተመሳሳይ በደል ሊታረም የሚችልበትን መንገድ ከመጠየቅ ችላ አይልም፡፡ ስለዚህ ያ ሰው ፍፁም ይቅርታን አግኝቻለሁ ብሎ በሰላም መኖር የሚችለው ከግል ተበዳይዋ፣ ከቤተሰቧ፣ ከማኅበረሰቡና ከመንግስት ይቅርታ ሲደረግለት ነው፡፡ በመንፈሳዊው ዓለምም ይኸው ነው፡፡ ሰው የግል ተበዳይን ብቻ ሳይሆን ቅዱስ እግዚአብሔርን ፍፁም ይቅርታ በሚጠይቅ ሰዓት ስርየትን ያገኛል፡፡ የአባቱን ሀብት ያባከነው ወጣት ወደቤቱ ሲመለስ ለአባቱ "በሰማይና በምድር ፊት በድያለሁ" ያለው ለዚህ ነው፡፡ በምድር ወላጅ አባቱን በሰማይ ያለ ፈጣሪውን በድሏልና፡፡ሉቃ 15
ስለዚህ በዚህ አግባብ ፍፁም የኃጢአት ይቅርታን ሊሠጥ የሚችል ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ ዳዊት " ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን አመስግኚ አጥንቶቼ ሁሉ የተቀደሰ ስሙን ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን አመስግኚ፤ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል ከደዌሽ ሁሉ የሚፈውስሽ…"
በማለት የይቅር ባይነት ሥልጣን የቅዱስ እግዚአብሔር መሆኑን ይገልፃል፡፡ ጨምሮም…ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ" እንዲሁም "አቤቱ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ አቤቱ ማን ይቆማል? ይቅርታ ከአንተ ዘንድ ነውና" በማለት ያስረግጣል፡፡መዝ 31፥1-5፣ መዝ102፥1-14፣መዝ 129(130)፥3
ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን የጌታ እግዚአብሔር መሆኑ ከታወቀ ኢየሱስ ክርስቶስ "ኃጢአትህ(ሽ) ተሰረየችልህ(ሽ)" ማለቱ እርሱ አምላክ(እግዚአብሔር) ለመሆኑ ጉልህ ማስረጃ ነው፡፡
ሉቃ7፥48፡- ሽቱ የቀባችውን ሴት በቃሉ "ኃጢአትሽ ተሰረዮልሻል በሰላም ሂጂ" ብሎ ሲያሰናብታት በዚያ   የነበሩ "ኃጢአትን ስንኳ የሚያስተሠርይ ይህ ማነው? እስከማለት ተገርመዋል፡፡
ሉቃ23፥43፡- በመስቀል ላይ ሳለ በቀኙ የተሰቀለ ወንበዴ በሰማይና በምደር የተፈፀሙ ተዓምራቶችን አይቶ "በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ" ብሎ ላቀረበው የይቅርታ ልመና" ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ" በማለት የይቅርታ ባለቤት መሆኑን አሳይቷል፡፡
ሉቃ24፥46፡-"…ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤በስሙም ንስሐና የኃጢአት ሥርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአህዛብ ሁሉ ይሰበካል"፡፡ ልናስተውል የሚገባን በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በዓለም ሃይማኖቶች ታሪክ ንስሐና የኃጢአት ሥርየት በስሙ የሆነ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ በቡድሐም፣ ሆነ በክሪሽና በዘራስተርም ሆነ በመሐመድ የለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም በቀደምት አበው ሆነ በነቢያት፣ በነገስታት ከጌታም በኋላ በተነሱ በሐዋርያት፣ ጻድቃን ሰማዕታት ስም የኃጢአት ሥርየት አልተሰበከም፡፡ ሁሉ በእርሱ ከኃጢአት ነፁ ለዚሁም ምስክር ሆኑ እንጂ፡፡
የሐዋ.ሥራ 2፥37-38፡- ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ጰራቅሊጦስ የሰበከውን የሰሙ ልባቸው የተነካ ሰዎች ምን እናድርግ ? ብለው በጠየቁ ሰዓት የተሰጣቸው መልስ "ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁ ይሠረይ ዘንድ በጌታ በእየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ" የሚል ነው፡፡
1ዮሐ1፥1-10፡- ያየነውን እንመሠክራለን ያለ ዩሐንስ ወንጌላዊ " …ኃጢአት የለብንም ብንል ውሸተኞች ነን … የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል…በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነፃን የታመነ ጻድቅ ነው፡፡" በማለት የኃጢአትን ይቅርታ እንዴት እንደሆነ ጽፎልናል፡፡
ኃጢአትን ይቅር የሚል በደልን የሚደመስስ ለሚወዱትም መንግሥቱን የሚያወርስ ጌትነቱ በሁሉ ላይ የሆነ በመጨረሻው ዘመን ግን የባርያን መልክ ይዞ የተገለጠ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ነው፡፡ ስለ ኀጢአታችን ብዙ ልንፆም፣ በፀፀት ልናለቅስ፣ በርካታ ምፅዋት ልንሠጥና በድካም እስክንዝል ልንሰግድ እንችላለን ፡፡ ይህ ሁሉ ግን ይቅርታውን ደጅ የምንጠናበት መንገድ እንጂ በራሱ ፍፁም ሆኖ ይቅርታን የሚያስገኝ አይደለም፡፡ ይቅርታን ለማግኘት ለኃጢአታችን መስዋዕት ሆኖ የቀረበ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን ልንበላ ክቡር ደሙንም ልንጠጣ የግድ ያስፈልገናል፡፡
መጽሐፍ "ያለ ደም ሥርየት የለም" እንዲል ጌታም በቃሉ "ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ህይወት አለው፡፡ ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ ሥጋዬን ካልበላችሁ ደሜንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም"፡፡ እንዲል ዕብ፣ዮሐ 6፥53
ጸሎት፡- ቅዱስ አምላክ ሆይ አናመስግንሀለን፡፡ ከቸርነትህ ገናናነት የተነሣ ሥጋህንና ክቡር ደምህን ለህይወት ለመድኃኒት እንዲሆነኝ ሰጥተኸኛል፡፡ ይህም በሕይወት ዘመኔ የተቀበልኩት በዋጋ የማይተመን እኔን የመውደደህ ስጦታ ነው፡፡ ቸር ሰውን ወዳጅ ሆይ ወደ ሕይወት መድኃኒት እንዳልቀርብ ዲያብሎስ በብዙ የምክኒያት ሰንሰለቶች አስሮኛልና ፍታኝ፡፡ ምክንያትን ቆርጬ የምጥልበትን ኃይል አድለኝ፡፡ በእኔም ዘንድ መኖርያህን ታደርግ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን!አሜን!
                                                    አቡነ ዘበሰማያት
ጥያቄ
1.ከኃጢአት የምትወደውና የተሰማማህ መተው እንዳለብህ ብታውቅም ለመተው የማትፈልገው ካለ ግለፅ?
2.አንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን እንዳንተ እምነት የኃጢአት ፍፃሜ ምንድን ነው?
3.ኃጢአትን መተውና ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ይቻላል ብለህ ታምናለህ?/በዚህ ዓለም/
4.መወሰን እየፈለግህ ያልወሰንክባቸው ጉዳዩች አለ? መቼ ትወስናለህ/ከመንፈሳዊ ህይወት ጋር በተያያዘ/
5. ይህቺ ዓለም ያለ ኃጢአት ምን ልትመስል ትችላለች?
 እውነትን በመመለስ ቢያንስ ለራስህ ታማኝ ሁን!
·         በሀገር ውስጥ ላላችሁ ልጆች እንደተለመደው መልሱን በወረቀት ጽፋችሁ ለሚቀጥለው ጉባኤ(የካቲት17) ትሰጣላችሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (6)


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!
እንኳን ለብርሃነ ልደቱና ጥምቀቱ አደረሳችሁ፡፡ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ዕረፍትም ረድኤትም በረከት ያሳድርብን አሜን!
ባለፉት ተከታታይ ትምህርታዊ ጹሑፎች አምላክ ልንለው የምንችለው አካል ሊያሟላ ስለሚገባው ባህርያት እያየን እዚህ ደርሰናል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ በሁሉ ሥፍራ የሚገኝ አምላክ ነው ስንል ምን ማለታችን ነው? የትኛውም ፍጡር በቦታ በጊዜና በሁኔታ የተወሰነ እንደሆነ የነገረ-መለኮት ሊቃውንትም ሆኑ የፍልስፍና ሊቃውንት ይስማሙበታል፡፡ በምድራውያንም ሆነ ለሰማያውያን ግዙፉንም ይሁኑ ረቂቃን ፍጥረታት በዚሁ የታጠሩ ናቸው፡፡
ሰማያውያን መላእክት እንኳ የልዑሉን ትዕዛዝ ለመፈፀም ሲተጉ አንዱን ሥፍራ ለቀው ወዳንዱ መሔድ ግድ ይላቸዋል፡፡ እንደሪቂቅነታቸው በረቂቅ ከተማ በሦስቱ ሰማያት ኢዮር፣ ራማና ኤረር ወስኖ አስፍሯቸዋል፡፡ ተልኳቸውን ከፈፀሙ በኃላ ወደዚሁ የመላእክት ከተማ ተመልሰው በምስጋና ይተጋሉ፡፡
ለልዑል እግዚአብሔር ግን እንዲህ አይደለም፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው እንደተናገረው     "ለመለኮት በታች ያለውን ለማንሳት ማጎንበስ ራስንም ማዘንበል ያለበት አይደለም በላይ ያለውን ያወርድ ዘንድ በፊትና በኋላ በቀኝና በግራ ያለውንም ለማቅረብ መዘዋወር የሚያሻው አይደለም፡፡ ሁሉ በእጁ የተያዘ ነው እንጂ" ቅዱስ ዳዊትም " ከመንፈስህ ወዴት እሔዳለሁ፤ ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ አለህ፤ ወደ ውቅያኖስም ጥልቅ ብወርድም በዚያ ትገኛለህ፤ እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ ከአጽናፍ አጽናፍ ብበርም እጅህ በዚያ ትመራኛለች ቀኝህም ትይዘኛለች" በማለት ስለ ልዑል እግዚአብሔር በሁሉ መገኘት ዘምሯል፡፡ መዝ139፥7-10፤ ቅዳሴ ማርያም
ቤተመቅደስን ያነፀ ሰሎሞንም በጌታ እግዚአብሔር ፊት ሲፀልይ…"ሰማያትም ከሰማያትም በላይ ያለ ሰማይ ሊይዙህ አይችሉም፡፡ እንግዲያው እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ?..."በማለት ገልጾታል፡፡ 1ነገ 8፥27
በኢሳይያስም "ሰማይ ዙፋኔ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት ለእኔ የምትሠሩልኝ ቤት እንዴት ያለ ነው? ሲል በሁሉ የመላ መሆኑን ገልጿል፡፡ ኢሳ66፡1፤ ማቴ 5፥34
በዘመኑ ፍፃሜ በመጽሐፍ ቅዱስ "በመጀመርያ ቃል ነበር፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበር ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለእርሱ አልሆነም" ተብሎ ልዕልናው ምልዓቱ ስፍሐቱ ከሀሊነቱ የተነገረለት አምላክ "ቃል ሥጋ ሆነ" ተብሎ ትህትናው ተገለጠ፡፡ ምልዓቱን ስፍሐቱን ሳይለቅ ባጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወሰነ፡፡ የሰውን አካልና ባህርይ በመንሳቱ በቦታ በጊዜና በሁኔታ የማይወስነው እርሱ በቦታ በጊዜና በሁኔታ ተወሰነ፡፡ ዮሐ1፥1-14
በቦታ ስንል ፤ በቤተልሔም ተወለደ፣ ወደ ግብፅ ተሰደደ፣ በናዝሬት አደገ፣ወደ ምኩራብ ገባ፣ ወደ  ኢየሩሳሌም ወጣ፣በቀራንዮ ተሰቀለ፣በጎሎጎታ ተቀበረ ወ.ዘ.ተ…ማለት ነው፡፡
በጊዜ ስንል፤ በ12 ዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፣ በ30ዘመን ተጠመቀ እርሱም ራሱ "ጊዜዬ ገና ነው" ብሎ እንደተናገረ የመሳሰሉትን ነው፡፡
በሁኔታዎች፤ ማለት ተፀነሰ፣ ተወለደ፣ ተሰደደ፣ ተራበ፣ተጠማ፣ ተገረፈ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ ፣ ተቀበረ ወዘተ… ማለታችን ነው፡፡
ነገር ግን ምንም እንኳ ከላይ ለተጠቀሱት ነገሮች ተገዢ ባይሆንም በፈቃዱ በእውነት በእነዚህ ስር ሆነ፡፡  ያም ሆኖ ግን ለእኛ የለበሰውን ደከማ ሥጋ ብቻ ሳይሆን ኃያል አምላክነቱን ፣አላዋቂ ሥጋን የተዋሀደ ሁሉን አዋቂነቱ፣ ራሱን ባዶ በማድረጉ ውስጥ ያለ ባለጠግነቱን (ሁሉ የእርሱ ከእርሱ በእርሱ መሆኑን) በውሱንነት የተጋለጠ አለመወሰኑን ወዘተ…በሥራውና በቃሉ ገለጠለን፡፡
በማኅፀነ ማርያም ያለተከፍሎ በምልዓት እያለ ሊወሰን ከምልዓቱ አልጎደለም፡፡ በምሳሌ ፀሐይ በጠፈር ሰማይ ሆና ብርሃኗ ወደምድር ሲመጣ በፀሐይቷ ዘንድ በምልዓት አንዳለ ከእኛ ዓይን እንዲዋሃድ፤ ጨለማውን እንደሚገፍ የተሰወረውን እንደሚገልጥ የእርሱም እንዲሁ ነው፡፡ ከሦስተንቱ አልጎደለም  አራት ወደመሆንም አልተጨመረም፡፡ ይህንም በቃሉ ሲያስረግጥ…"ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደሰማይ የወጣ የለም ይኸውም በሰማይ ያለ የሰው ልጅ ነው" ብሏል፡፡ ዮሐ 3፥13 ይህን በተናገረበት ቅፅበት በኒቆዲሞስ ፊት ያለ እርሱ እንደምን በሰማይ ያለ የሰው ልጅ ነው ሊል ይችላል? ምልዓቱን(በሁሉ ቦታ መገኘቱን) ለመግለፅ ካልሆነ በቀር፡፡
ለሐዋርያትና በስሙ ላመን ክርስቲያኖች ሁሉ በገባልን ቃልም እንዲህ ብሏል፡-
ማቴ18፥20 …በስሜ ሁለትና ሦስት ባላችሁበት በመካከላችሁ እሆናለሁ፡፡
ማቴ28፥19… አባቴ አንደላከኝ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ፡፡ ሂዱና አህዛብን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ያዘዘኳችሁንም እያስተማራችሁ ደቀመዛሙርቴ አድርጓቸው፡፡ እነሆ እስከዓለም ፍፃሜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡
ይልቁንም ቅዱስ ጳውሎስ ለቈላስዩስ ሰዎች በላከው መልዕክቱ " የመለኮቱ ሙላት በሥጋው ተገልጦ ይኖራል " እንዳለ በለበሰው ሥጋ በመለኮታዊ ሥልጣን በአባቱ ዙፋን በአባቱ ክብር ተቀምጦ ራቂቁንም ሆነ ግዙፉን ዓለም የሚታየውንም ሆነ የማይታየውን እንደሚገዛ እንዲሚጠብቅ እንደሚያስተዳድር ገልጿል፡፡ቆላ 2፥9
ዳግመኛም ሲመጣ በክበበ ትስብዕት በግርማ መለኮት ይመጣል፡፡ ይህም ማለት በክበበ ትስብዕት የተወጋ ጎኑ፣ የተቸነከሩ እጆቹ እግሮቹ እየታዩ ይመጣል፡፡ ምንም እንኳ በክበበ ትስብዕት ቢሆንም እነደ አምላክነቱ ሁሉ እኩል ያየዋል፡፡ በኋላ በቀኝ በግራ የሚሆን የለም አንዱ ቀርቦ አንዱ ርቆ አንዱ ከጀርባ አንዱ ከጎን ሆኖ አያያውም፡፡ ለሁሉ በእኩል ከፊቱ ሆኖ ይመለከተዋል አንጂ፡፡ ምን የአዳም ዘር በዝቶ እንደ እንድጽፍቀተ ሮማን ቢጨናነቅ ሁሉ በእኩል ርቀት በአንድ ዓይነት በፊቱ ያየዋል፡፡ ይህም ግዙፍ ሲሆን ረቂቅ ውሱን ሲሆን ምሉዕ አምላክ መሆኑን በተረዳ ነገር ያሳያል፡፡
ልዑል ሲሆን ሳለ ትሁት ሆኖ ራሱን በምንችለው መጠን የገለፀልን፤ ይወዳጀን ዘንድም ፍቃዱ የሆነ ጌትነቱን ፈጣሪነቱን የባህርይ አማላክነቱን አምነን እንመስክር ዘንድ የመረጠን የነገሥታት ንጉሥ የጌቶች ጌታ የአማልክት አምላክ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ቸር ከሆነ ከሰማያዊ አባቱ አዳኝ ርኅሩኅ ከሆነ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ክብር ምስጋና ይግባው፡፡
ለዘለዓለሙ አሜን!

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (5)


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን የሚያውቅ የባህርይ አምላክ ስለመሆኑ፤
መግቢያ፡- ባለፉት ሳምንታት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ሁሉን ቻይ" አምላክ መሆኑን በተረዳ ነገር አይተናል፡፡ በዛሬው ጹሑፋችን አምላካዊ ባህርያት ከሆኑት አንዱን "ሁሉን ማወቅ" ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ በማስደገፍ እናያለን፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምስጢሩን ይግለጽልን!
ሁሉን ማወቅ የእግዚአብሔር የብቻው /የተለየ/ ባህርዩ ነው፡፡ በሰማይም ሆነ በምድር ወይም በውቅያኖስ፣በብርሃንም ሆነ በጨለማ ፣ በቁሳዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ዓለም እርሱ የማያውቀው ከእርሱ ተሰውሮ የሚፈጸም አንዳች ስንኳ የለም፡፡ ሁሉንም ከመሆኑ በፊት እንደተደረገ አድርጎ ያውቀዋል፡፡ በጸሎተ ኪዳን እንተፃፈ " እምቅድመ ህሊና ኲሎ የአምር፣ ወእምቅድመ ህሊና ይፈትን" ከህሊና አስቀድሞ ያውቃል፣ ከሀሳብም ቀድሞ ይመረምራል፡፡ ዓለምን ጅማሬው ላይ ሆኖ ፍፃሜውን ያውቀዋል፡፡ በአጭር ቃል ከእርሱ ምንም ምን አይሠወርም የክፍዎችንም ሆነ የበጎዎችን ምክር ያውቃል፣ የጠቢባንንም አሳባቸውን ይመረምራል፡፡ ከመሆኑ አስቀድሞ እንጂ ከተደረገ በኋላ ተመራምሮ በነገሩ የሚደርስ አይደለም፡፡ በመሆኑም አኛንም ማንም ከሚያውቀን ይልቅ ከራሳችንም በላይ ያውቀናል በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ተብሏል፡፡
1ሳሙ 2፥3 " አትታበዩ በኩራትም አትናገሩ፡ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና…"
1ኛ ዮሐ 3፥20 " እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል"
ይህ እንዲህ ከሆነ "ሁሉን አዋቂነት" የሚለው ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀፀል ይችላል ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምላሽ "በትክክል" የሚል ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ እነሆ፡፡
ማቴ9፥1-8 ጌታ እየሱስ ክርስቶስ በአልጋ የተኛ ሽባ ወደ እርሱ ባመጡ ጊዜ ሽባውን"አንተ ልጅ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ" አለው፡፡ ከጻፎች ግን አንዳንዶቹ በልባቸው ይህስ ይሳደባል አሉ፡፡ ኢየሱስም አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ ስለምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ?...
ማቴ 12፥15 ጌታችን በሰንበት ስለፈወሰ ፈሪሳውያን ሊገድሉት ሲማከሩ ምክራቸውን አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ ይላል፡፡
ማቴ 12፥22-27 ሕዝቡ በአጋንንት ላይ ባለው ሥልጣን ሲደነቁ ፈሪሳውያን ግን በአጋንንት አለቃ በብዔል ዜቡል አጋንንትን ያወጣል በማለት ሲያስቡ ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው እርስ በርሷ የምትለያይ መንግስት አትፀናም…
ማቴ 17፥24-27 ቀረጥ ሰብሳቢዎች ጰጥሮስን በውጭ አግኝተው መምህራችሁ ግብር አይገብርምን? ብለው ሰለጠየቁት ጴጥሮስ ይህን ሊናገር ወደ ቤት ሲገባ አስቀድሞ የሆነውን አውቆ ዓሣ አጥምዶ ያገኘውን እንዲከፍል ነግሮታል፡፡
ሉቃ 5፥1-11 ቅዱስ ጴጥሮስ ሌሊቱን ደክሞ ያልሆነለትን በጌታችን ትዕዛዝ ብዙ ዓሣ በመያዙ ቢደሰትም በታላቅ ፍርሃት ጌታን "እኔ ኃጥአተኛ ሰው ነኝና ከእኔ ተለይ" ብሎታል፡፡ መተርጉማን ይህን የቅዱስ ጴጥሮስን ቃል ሲፈቱት የባህሩን ውስጥ እንዲህ ያወቀው የእኔንማ ልብ እንዴት ይመረምረው ብሎ እንደፈራ ያትታሉ፡፡
ሉቃ 7፥36-50 መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስምዖን ፈሪሳዊ ቤት ለምሳ በተቀመጠበት ወቅት ባለ ሽቶዋ ማርያም እግሩን እየሳመች በእንባዋ እያጠበችና በፀጉርዋ እያበሰች ሽቶ ቀብታ ሰለኃጢአቷ ሥርየት በአርምሞ ስትማፀ ስምዖን ፈሪሳዊ አይቶ ይህስ ነብይ ቢሆን ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደሆነች እንዴትስ እንደነበረች ባወቀ ነበር ኃጥአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ፡፡ለዚህ ሰው የልቡን አውቆ  ምን ዓይነት አስደናቂ መልስ እንደሰጠው ቃሉን አንብብ፡፡
ሉቃ 8፥43-48 12 ዓመት ደም ይፈሳት የነበረች ሴት የነበረች ሴት ጌታን ህዝቡ እያገፋው ሳለ ተሰውራ የቀሚሱን ዘርፍ በመንካቷ ተፈወሰች ጌታም ማን ነው የነካኝ ብሎ ሲጠይቅ ሐዋርያት ህዝቡ ይገፉሃል ማነው የነካኝ ትላለህን? ሲሉት አንድ ሰው ዳሶኛል ኃይል ከእኔ እንደወጣ እኔ አውቃለሁና ብሎ ነው የመለሰው ሴቲቱም እንዳልተሠወረች ባየች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች የተደረገላትንም በህዝቡ ሁሉ ፊት መሠከረች፡፡
ሉቃ 22፥31-34 ጌታችን እንደሚያዝና ሁሉም ጥለውት እንደሚሸሹ በተናገረበት ምሴተ ሐሙስ ቅዱስ ጴጥሮስ ሌሎች ቢክዱህ እኔ አልክድህም ብሎ ለሠጠው የትምክህት መልስ" ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ እንደሚክደው ቀድሞ ነግሮታል፣ ይኸውም እንደቃሉ ተፈፅሟል፡፡
ዮሐ2፥5 " ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፡፡ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና፡፡
ዮሐ 1፥47-50 ፊልጶስ ናትናኤልን ጋብዞ ወደ ጌታችን ባመጣው ሰዓት ጌታ "በልቡ ተንኮል የሌለበት የእስራኤል ስው እነሆ" በማለቱ ናትናኤል ከወዴት ታውቀኛለህ? ቢለው ፊልጶስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች አየሁህ የሚል መልስ ሲሰጠው" መምህር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ" በማለት እርሱ ሁሉን አዋቂ አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን መስክሯል፡፡
ዮሐ4፥1-መጨረሻ  በተፃፈው ፍፁም የሚመስጥ ታሪክ ሳምራዊቷ ሴት ለሀገሯ ሰዎች ከጌታችን ጋር ስለነበራት ቆይታ ስትገልፅላቸው ወደ እርሱ እንዲመጡም ስትጋብዛቸው "ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ…" ብላለች ቁጥር 29
ዮሐ6፥15 እንጀራ በልተው ሲጠግቡ እርስ በርሳቸው ከሆነስ አይቀር ስንራብ እያበላ ፣ስንጠማ እያጠጣ፣ስንታመም እየፈወሰ፣ስንሞት እያሰናዳ ቢገዛን መልካም በሆነ ኑ እናንግሠው ብለው ያሰቡትን አውቆ ከአጠገባቸው ፈቀቅ ብሎ ወደ ተራታ ወጣ ይላል፡፡
ዮሐ11፥1-መጨረሻ ፡- በቦታው በአካል ባይገኝም ስለአልዓዛር መታመምና መሞት ቀድሞ ለሐዋርያት ነግሯቸዋል፡፡
v  ጌታችን ስለሞቱና ትንሣኤው አስቀድሞ ተናግሯል፡፡
ማቴ 24፥1-መጨረሻ፡- የዓለም መጨረሻና የዳግም ምፅዓቱ ምልክቶችን አስቀድሞ ተናግሯል፡፡        ዮሐ16፥29-30 ሐዋርያት"እነሆ አሁን በግልጥ ትናገራለህ፣በምሳሌም ምንም አትናገርም ሁሉን እንድታውቅ ማንምም ሊጠይቅህ እንዳትፈልግ አሁን እናውቃለን፡፡
ዮሐ21፥15-17 በጥብርያዶስ ባህር ዳርቻ ጌታችን ከስምዖን ጴጥሮስ ጋር በነበረው ቆይታ "ትወደኛለህን?" ብሎ ሦስት ጊዜ ለጠየቀው ጥያቄ የሰጠው የመጨረሻ ምላሽ "ጌታ ሆይ አንተ ሁሉን ታውቃለህ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ " የሚል ነው፡ በዚህም ሁሉን አዋቂ መሆኑን አስረግጦ መስክሯል፡፡ በመቀጠል ጌታችንም ቅዱስ ጴጥሮስ በኔሮን ቄሣር ዘመን በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔር ያከብር ዘንድ እንዳለው ነግሮታል ይህም ሁሉን አወቂ መሆኑን ያስረገጠበት መንገድ ነው፡፡
ራስን መመዘኛ /መመርመርያ/ ጥያቄ!

.የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አዋቂነቱ በእኔ ሕይወት ውስጥ ያለው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው?
ለ. በእርግጥ እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ መሆኑን በእውነት አምናለሁ?
. እግዚአብሔር ከሁሉን አዋቂነቱ ወሰን ተሠውሬ ኃጢአት ሠርቼ አውቃለሁን?
መ. ቅዱስ እግዚአብሔር / ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ / ከልቤ ጋር ያለው ግንኙነት ምን ያህል ነው? እንዴትስ እረዳዋለሁ?

v  በሀገር ውስጥ ላላችሁ ለጥያቄዎቹ መልስና ሀሳባችሁን በሪፖርት(በወረቀት) በጉባኤ ቀን ትሰጣላችሁ፡፡
ይቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (4)


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
       በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!
መግቢያ
        የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ቻይነቱ በሞት ላይ በነበረው ሥልጣንም ገልጿል፡፡ ሞት የኃጢአት ውጤት(ደመወዝ) ነው፡፡ ለሞት ያልተገዛ ፍጥረትም የለም፡፡ ከአዳም ጀምሮ የአዳማዊው ተፈጥሮ ተጋሪ የሆኑ ልጆቹና ለአዳም የተፈጠሩት ፍጥረቶች ሁሉ በሞት ጥላ ሥር ወድቀዋል፡፡ ርዕሳነ አበው፣ነብያት፣ነገሥታት፣ካህናት፣ሁሉ በሞት መዳፍ ተያዙ ማምለጥም የታቻለው ወይም ይህን የሞት ፍርድ ሊያስቀር የቻለ አንድ ስንኳ አልተገኘም፡፡
ይህንኑ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ምዕ 5፥12-21 በጥሩ ሁኔታ አብራርቶታል፡፡ "…ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት… ነገር ግነ በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ…" ጨምሮም "…የኋላኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤ ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና፡፡ነገር ግን ሁሉ ተገዝቶአል ሲል ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው" ፡፡ 1 ቆሮ 15፥25-28 በማለት የሞትን ሥልጣንና የሞትን ሥልጣን ሰብሮ ኃያልነቱን(ሁሉን ቻይነቱን) የገለፀውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥራ ግልፅ አድርጓል፡፡
      አበው ለብዙ ዘመናት ከዚህ የሞት ባርነት ነፃ ሊያወጣቸው ወደሚችል በብዙ ልመና ሲቃትቱ ኖረዋል፡፡ ጊዜው ሲደርስ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ሞትን ሻረው፡፡ ሞት ነግሦባት በነበረች ምድር ለመጀመርያ ጊዜ " እሰቀላለሁ፣ እሞታለሁ በሦስተኛውም ቀን እነሳለሁ" እንዲሁም " ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል እኔ በፍቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ፤ይህቺን ትዕዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ፡፡" በማለት ሞትን ያስደነገጠ የአዳምን ተስፋ ያረጋገጠ አዋጅ ተሰማ፡፡ ዮሐ 10፥18፣ ማቴ 16፥21
     መግደልና ማዳን የእግዚአብሔር ብቻ ሥልጣን መሆኑ በቅዱሳት መጻሕፍት የተረጋገጠ ነው፡፡ ኦሪ.ዘዳ 32፥39፣ 1ሳሙ 2፥6፣ ማቴ 10፥28-31 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን "ነፍሴን ላኖራትም ላነሣትም ሥልጣን አለኝ" በማለት በሞት ላይ ያለውን ገዢነቱን በተጨማሪም የመግደልና የማዳን መለኮታዊ ሥልጣን ያለው ወይም እርሱ እራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ገለፀ፡፡ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በለየባት በዚያች ሰዓትም የተናገረውን አስተውል፡፡ "ኢየሱስም በታላቅ ድምጽ ጮኾ አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ፡፡" ይህ ጩኸት ይህ ቃል የሞትን ሥልጣን ያረጋገጠ የዲያቢሎስ መንግስት የቆረጠ ነው፡፡ ሉቃ 23 ፥46
ልዩ ከምትሆን ቅድስት ትንሣኤው በፊትም በኢየሩሳሌም አውራጃዎች እየተዘዋወረ ሲያስተምር ሙታንን በማስነሳት እርሱ በሞት ላይ ፍፁም ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑን አሳይቶናል፡፡
-    ሉቃ 8፥49-56 ፡- ኢያኢሮስ የተባለው የምኩራብ አለቃ ልጁ በሞተችበት ወቅት ጌታችን በቃሉ አስነስቷታል፡፡ "አንቺ ብላቴና ተነሺ" ብቻ በማለት

-    ዮሐ 11፥1-44 ፡- የጌታ ወዳጅ አልዓዛር ሞቶ በተቀበረ በአራተኛው ቀን ጌታችን ትንሣኤና ሕይወት እርሱ መሆኑንና በእርሱ የሚያምን ቢሞትም እንኳ ህያው እንደሚሆን ካወጀ በኋላ ወደመቃብር ሔዶ "አልዓዛር ሆይ ወደ ውጭ ና" በማለት አስነስቶታል፡፡
በዚህ ላይ ምናልባት አንዳንዶች ነቢያት፣ሐዋርያት ድውይ ፈውሰዋል፣ምውት አንስተዋል ይህን አደረጉ ብለን "ሁሉን ቻይ" እንደማንላቸው ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስንም እንዲሁ ነው ብለው ሊከራከሩ ይችላሉ፡፡ 1ኛነገ 17፥17-24፣ 2ኛ ነገ 4፥32-37፣ ሐዋ.ሥራ 9፥40
መልስ
1ኛ- ነቢያትም ሆኑ ሐዋርያት ሙት እስከማንሳት የደረሱት ከልዑል እግዚአብሔር በተሠጣቸው ሥልጣን ጾመው፣ ጸልየው፣ ወድቀው፣ ተነስተው ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች የሚያመለክቱትም ይህንኑ ነው፡፡ ማር16፥17፣ ሉቃ 10፥17-20፣ዮሐ 14፥12-14፡ እውነት እውነት እላችኋለው በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፣ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል… ማናቸውም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ፡፡ ያለውን ቃልኪዳን ይጠብቅላቸዋል፡፡ የእርሱ ግን መጾም፣መጸለይ፣ መውደቅ፣መነሣት ሳያስፈልገው በሥልጣኑ ነው፡፡
2ኛ- ከነቢያትም ሆነ ከሐዋርያት ሙት እስከማንሳት የደረሱ ሁሉ በመጨረሻ እነርሱ ራሣቸው በሥጋ ሞት ተይዘዋል፡፡ ጌታችን በትንሣኤ ዘጉባኤ እስኪያስነሳቸውም ይጠብቃሉ፡፡ሙት ያስነሱ እነርሱ ለራሳቸው ግን አስነሺ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እርሱም ትንሣኤ ሕይወት የተባለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ለእርሱ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ ይህንኑም ለማስረዳት ነው ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በለየባት ሰዓት እንኳ ብዙ ሙታን ተነስተው በኢየሩሳሌም የታዩት፡፡ በማቴ 27፥51-54 መላእክትም ለሴቶቹ " ሕያዋን ከሙታን መካከል ስለምን ትሹታላችሁ እርሱ በዚህ የለም ተነሥቶአል" ያሉአቸው፡፡ ሉቃ 24፥6
         በእነዚህ ከብዙ በጥቂቱ አእምሮን ለማንቃትና እምነትን ለማፅናት ከተጠቀሱት በተጨማሪ ብዙ የመፅሐፍት ቅዱስ ክፍሎችና የአበው ትምህርት ሁሉን ቻይነቱን አምልተው አስፍተው ገልፀውታል፡፡ ያን በማንበብና በማስተዋል የበለጠ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በሚቀጥለው አምላካዊ ባህርያት ከሆኑት "ሁሉን አዋቂ" ስለመሆኑ ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም እንማራለን፡፡
ይቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ጥቅምት 2005